የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሹመትን አፅድቋል።
በዚህ መሰረትም ምክር ቤቱ ከቀረቡት 88 እጩዎች ውስጥ ዶክተር ዳንኤል በቀለ ባላቸው የትምህርት ዝግጅትና የስራ ልምድ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ሆነው እንዲሾሙ አፅድቋል።
ዶክተር ዳንኤልን በቀለ ሹመቱ የተሰጣቸውም ከዚህ በፊት የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር በመሆን ሲያገለግሉ የቆዩትን ዶክተር አዲሱ ገብረ እግዚአብሔርን በመተካት ነው።
ዶክተር ዳንኤል ከኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽርነት ባሻገር፣ ጎን ለጎን ሌላ ስራ እንዲሰሩ በምክር ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ የቀረበው ሀሳብ ውድቅ ተደርጎ በመጨረሻ ተሿሚው በምክር ቤቱ ፊት ቀርበው ቃለ መሐላ ፈፅመዋል።
ከኦክስፎርድ ዩኒቨርሲቲ በአለም አቀፍ ህግ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን የያዙት ዶክተር ዳንኤል በተለያዩ መንግስታዊና አለም አቀፍ ድርጅቶች ከሰብአዊ መብት ጉዳይ ጋር በተያያዘ አገልግለዋል፡፡
ዶክተር ዳንኤል በአፍሪካ የአለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ፣በህብረት ኢንሹራንስ የህግ ክፍል ዋና ዳይሬክተር፣ በኢትዮጵያ የአክሽን ኤይድ የጥናትና ምርምር ሃላፊ በመሆን አገልግለዋል።
ከዚህ ባለፈም በኦክስፋም፣በፓክት፣ዩ ኤስ ኤይድና በአለም ባንክ በተሰኙ የተለያዩ ድርጅቶች ውስጥ በአማካሪነት ሰርተዋል።
ዶክተር ዳንኤል በቀለ በተለያዩ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ላይ ጠንካራ ተሳትፎ በማድረግ በዓለም አቀፍ ደረጃ ድህነትን ለመቀነስ በሚደረገው ጥረት ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ አበርክተዋል።