የታላቁ የህዳሴ ግድብ 11 ሃይል ማመንጫዎች ጣቢያዎች (power unit) ተከላ በመጪው መስከረም ይጀመራል ተባለ።
የ11ዱ ኃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ተከላ ሲኖ ሃይድሮ በተባለው ስራ ተቋራጭ አማካኝነት የሚከናወን ነው።
ከአምስት ወራት በፊት በፕሮጀክት ሳይቱ ስራ የጀመረው ሲኖ ሃይድሮ ከፊሎቹ የሃይል ማመንጫ ጣቢያ አካላት በቻይና በመመረት ላይ መሆናቸውን አስታውቋል።
በአገር ውስጥ ሊገጣጠሙ እና ሊመረቱ የሚችሉት የሃይል ማመንጫ ጣቢያዎቹ ክፍሎችም በግድቡ የግንባታ ሳይት ይመረታሉ ነው የተባለው።
በቻይና የሚመረቱት የሃይል ማመንጫ ጣቢያዎች አካላት፣ የውሃ ማንደርደሪያ፣ ተርባይን አቃፊ ግዙፍ ብረቶች እና ሌሎች ግብዓቶች ናቸው።
የማመንጫ ጣቢዎቹ አካል የሆኑ ግዙፍ ብረቶች በያዝነው ወር ከቻይና ወደ ኢትዮጵያ መጓጓዝ እንደሚጀምሩም ታውቋል።
የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት ዋና ስራ አስኪያጅ ኢንጂነር ክፍሌ ሆሮ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንዳሉት፥ የኃይል ማመንጫ ጣቢያዎቹ ተከላ በመጭው መስከረም ወር ይጀመራል።
በ2013 ዓ.ም ከታላቁ የህዳሴ ግድብ የመጀመሪያውን የኤሌክትሪክ ሃይል የሚሰጡት ሁለቱ የቅድመ ሃይል ማመንጫ ጣቢያዎች ተከላም፥ በፈረንሳዩ አልስቶም ኩባንያ አማካኝነት በመተከል ላይ ናቸው።
750 ሜጋ ዋት የኤሌክትሪክ ሃይል የሚያመነጩት የቅድመ ሃይል ማመንጫ ጣቢያዎቹ ተከላ አሁን ላይ የውሃ ማንደርደሪያ አካላት ገጠማ እና ብየዳ ላይ ደርሷል።
በተከለሰው የፕሮጀክት መርሃ ግብር መሰረት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ፕሮጀክት በ2015 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ ይጠበቃል።