ለህገ-ወጥ የጦር የመሳሪያ ዝውውር መፍትሄ ለማበጀት ዓለም አቀፍ ልምድ ካካበቱ ተቋማት ጋር እየተሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ሚኒስትሯ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ ዴሞክራሲን ለመገንባት በምታደርገው ጥረት የተለያዩ ፈተናዎች እየገጠሟት ነው። ዴሞክራሲን ያለ ህግ የበላይነት ማረጋገጥ ደግሞ አይቻልም።
ከዚህ አንጻር ባለፉት ጊዜያት የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የተቋማት የአቅም ግንባታ ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውሰዋል።
ይሁንና በተለያየ ጊዜ የተለያዩ ፈተናዎች እያጋጠሙ እንደነበር፤ በቅርቡ የተፈጸመው የከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት ግድያ የዚህ አንዱ አካል መሆኑን አንስተዋል።
መቆጣጠር ባይቻል ችግሩ ይበልጥ የከፋ ይሆን እንደነበር በመጠቆምም ዜጎች ስጋት ሊገባቸው እንደማይገባ ከጸጥታ አካሉ ጎን በትብብር በመስራትም መሰል ጥቃቶችን እንዲያከሽፍ ጠይቀዋል።
የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደቱ በቀጣይም ችግር ሊገጥመው ይችላል የሚሉት ሚኒስትሯ ይህ እንዳይሆን መስራት የሁሉም ኃላፊነት መሆኑን ያስገነዝባሉ “አገር የሚገነባው እያንዳንዱ ሰው ኃላፊነት ሲወስድ ነው” በማለት።
ከዚህ ባሻገር እየታዩ ያሉ ችግሮችን ለማረም በህገ-መንግስቱ መሰረት የጸጥታ ኃይሉን የማደራጀት ስራ እየተከናወነ መሆኑን፤ ሲጠናቀቅ ይፋ እንደሚሆንና የሚመለከታቸው አካላት እንደሚመክሩበት ተናግረዋል።
የህዝቡን ሰላም እያወኩና ስጋት ላይ እየጣሉ ከሚገኙ ወቅታዊ ችግሮች አንዱ የሆነውን ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር በተመለከተም በአጭርና በረጅም ጊዜ ዕቅድ የመፍትሄ እርምጃዎችን ለመውሰድ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
እየተዘጋጀ ካለው የህግ ማዕቀፍና በመግቢያና መውጫ በሮች እየተካሄደ ካለው ቁጥጥር ባሻገር በዘመናዊ ቴክኖሎጂ የተደረገፈ ስራ እየተከናወነ መሆኑን አስታውቀዋል።
በህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ላይ የካበተ ልምድ ካላቸው ዓለም አቀፍ ዩኒቨርሲቲዎችና የምርምር ተቋማት ጋር ለመስራትም ውይይት መጀመሩን ገልጸው ''የጥናት ውጤቶችን የማግኘትና የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ በዝርዝር ለማጥናት እየሰራን ነው'' ብለዋል።
እነዚህ ሁኔታዎች መልክ ሲይዙና ህግ ሲከበር የሰላምና ደህንነት እንዲሁም የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደቱ ላይ ለውጥ እንደሚመጣ የሚያምኑት ሚኒስትሯ እነዚህ ስራዎች ለቀጣይ መደላድል ይፈጥራሉ፤ የአስተሳሰብ ለውጥ ላይ የሚሰራው ስራ ጊዜ የሚወስድ ቢሆንም የሁሉም መሰረት ነው ይላሉ።
"የሰላምና የደህንነት ስራችን ዜጎችን ማዕከል ያደረገና ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ያከበረ ይሁን ነው ያልነው” የሚሉት ሚኒስትሯ መንግስት ኢ-ዴሞክራሲያዊ ለሆኑ ድርጊቶች ምላሽ ለመስጠት ከአንዳንድ ወገኖች እንደሚሰማው የትኩረት ወይም የአቅም ማነስ የለበትም ባይ ናቸው።
"መንግስት ህግ የማስከበር ስልጣኑም አቅሙም አለው። የዴሞክራሲ ግንባታ ሂደቱን ሊጎዳ ይችላል በሚል ነበር፤ ነገር ግን የሚታየው ምላሽ ይህን የሚያግዝ ባለመሆኑ ህግ የማስከበር ሚናው ላይ ያተኩራል" ብለዋል።
ወይዘሮ ሙፈሪያት "በዴሞክራሲ ግንባታ ቀደም ሲል ከመጣንበት ሂደት አንጻር የነበሩ ጠንካራ ጎኖችን የበለጠ በማጠንከር፤ ድክመቶችን ደግሞ በማያዳግም ሁኔታ ለማረም የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው" ሲሉም ሃሳባቸውን ያጠናክራሉ።
ያለፈው አንድ ዓመት ጉዳቶች ያጋጠሙበት ቢሆንም ጥሩ ትምህርትም ተገኝቶበታል በማለት ከነበረው ሂደት ትምህርት ተወስዶ በተገቢው ልክ ህግ የማስከበር ስራ እንደሚሰራ ገልጸዋል።
"ይህ ሲሆን ግን ስናልፍ ስናገድም ማስፈራራት ሳይሆን የግንዛቤ ስራችንን እየቀጠልን፤ አገርን ወይም ዜጎችን የሚጎዱ ግለሰቦችና ቡድኖች ደግሞ በህጉ መሰረት እያረምንና ተጠያቂነትን እያረጋገጥን መሄድ ነው ቀጣይ አቅጣጫችን" ብለዋል።