15 Jul
15Jul

ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ዓመታዊ ወታደራዊ ልምምዳቸውን ጀመሩ።

ልምምዱ አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ወታደራዊ ልምምድ ለማድረግ የደረሰችው ስምምነት ሲሆን፥ በዛሬው እለትም የአሜሪካ መከላከያ አባላት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሃይል ጋር በጥምረት ልምምድ ማድረግ ጀምረዋል።

ልምምዱ በሶማሊያ በተሰማራው የአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ሃይል (አሚሶም) አባላትን አቅም ማሳደግ ላይ ያተኮረ ሲሆን፥ ወደ 1 ሺህ 100 የሚጠጉ ወታደራዊና የመንግስት ሃላፊዎች ይሳተፉበታል።

ልምምዱ የመከላከያ አባላትን ዝግጁነትና አቅም በማሳደግ ሰላምን ለማስከበር የሚደረገውን ጥረት እንዲደግፉና በቀጠናው ሰላምን ለማስፈን እንደሚያግዝም ታምኖበታል።

ከዚህ ባለፈም ሽብርተኝነትና የእርስ በርስ ግጭቶችን ቀድሞ ለመከላከል እንደሚያስችልም ተገልጿል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስትር ዲኤታ አቶ ፍስሃ ወልደሰንበት፥ ልምምዱ በቀጠናው የተሻለ መረጋጋት ለመፍጠር እንደሚያግዝ ተናግረዋል።

የሰላም ማስከበር ተልዕኮ ዓለም አቀፋዊ ጉዳይ በመሆኑ በመሰል ስልጠናዎች አቅምን ማሳደግ እንደሚገባ የልምምዱን መጀመር አስመልከቶ በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተነስቷል።

ዛሬን ጨምሮ ለ16 ቀናት በሚቆየው ልምምድ፥ ከብራዚል፣ ብሩንዲ፣ ካናዳ፣ ጂቡቲ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣሊያን፣ ኬንያ፣ ኔዘርላንድስ፣ ሩዋንዳ፣ ሶማሊያ፣ ኡጋንዳ እና ዩናይትድ ኪንግደም የተውጣጡ ወታደሮች ይሳተፋሉ።

ከዚህ ባለፈም እንደ አፍሪካ ህብረትና እና የአሜሪካ ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት፣ የአሜሪካ የሰላም ተቋምና ከዓለም አቀፉ ቀይ መስቀል ማህበር የተውጣጡ ባለሙያዎችም ይሳተፋሉ ነው የተባለው።

በተያያዘም ኢትዮጵያና አሜሪካ በህክምና ዝግጁነት ላይ ያተኮረ ልምምድ እያደረጉ ነው።

ይህ ልምምድ ወታደራዊና መደበኛ የህክምና አባላት የሚሳተፉበት ሲሆን፥ የልምድ ልውውጥ ለማድረግና የሚሰጠውን የህክምና ክትትል አቅም ለማሳደግ ያስችላል ነው የተባለው።

በመንግስታቱ ድርጅት እና በአፍሪካ ህብረት ሰላም አስከባሪ ውስጥ የጎላ ድርሻ ያላት ኢትዮጵያ ከሁለት አመት በፊት ከአሜሪካ ጋር መሰል ወታደራዊ ልምምድ ማድረጓ ይታወሳል።

Comments
* The email will not be published on the website.
I BUILT MY SITE FOR FREE USING