09 Jul
09Jul

"ማህበራዊ እሴቶች ግጭትን የመከላከል አቅማቸው ከፍተኛ በመሆኑ ያሉትን ማዳበር፤ አዳዲሶችንም መገንባት ይገባል" አሉ የሰላም ሚኒስትሯ ወይዘሮ ሙፈሪያት ካሚል።

ሚኒስትሯ ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ጋር ባደረጉት ቃለ-ምልልስ እንዳሉት ሰላም በእያንዳንዱ ግለሰብ እጅ ያለ ጉዳይ ነው።

በእጃችን ያለውን እንዴት በአግባቡ እንጠቀም የሚለው ደግሞ ከእሴቶቻችን ጋር የተቆራኘ ነው ይላሉ።

"ሰላም ከራስ ይጀምራል፤ ለራስም ሆነ ለሌሎች በጎ ማሰብ ያስፈልጋል የሚሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት የኢትዮጵያዊያን እሴቶች ይህን ማድረግ የሚያስችሉ መሆናቸውን ይገልጻሉ።

ሰላም በዋናነት በማህበረሰቡ የሚገነባ ነው፤ የጸጥታ ሃይሉ ግጭቶች ሲኖሩ ወይም ማህበረሰቡ ያጎደላቸውን ነው የሚያስተካክለው በማለት ሁሉም ዜጋ ለሰላም የማይተካ ሚና እንዳለው ያሰምሩበታል።

መነጋገር፣ መደማመጥ፣ መከባበር፣ መስጠት፣ እና ሌሎችም ሰላም ለመገንባት ቁልፍ ሚና ያላቸው ማህበራዊ እሴቶች ናቸው።

ከእሴቶቻችን መካከል የነበረን፣ አሁን እየጎደለን ያለውና በትልቁ ልናዳብረው የሚገባው መደማመጥን ነው ይላሉ ሚኒስትሯ ታላላቆች ብቻ ሳይሆን ታናናሾችም ሊደመጡ እንደሚገባ አጽንኦት በመስጠት።

የሰላም ሚኒስትሯ እንዳሉት መከባበርም ሌላው ለአብሮነት ቦታ ያለውና ግጭትን የሚከላከል ማህበራዊ እሴት ነው።

መስጠት እንደ መውሰድ በሃይና በጉልበት የሚፈጸምና ለግጭት የሚዳረግ ሳይሆን የእርካታ ምንጭ ነው የሚሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት መዳበር አለባቸው ብለው ከጠቀሷቸው እሴቶች መካከል መድበውታል።

እንደ እርሳቸው አነጋገር "መስጠት ውስጥ ሰላም አለ፤ ኢትዮጵያዊነት ውስጥ ደግሞ ንፉግነት የለም"፤ በመሆኑም መስጠት ግጭትን የማምከን አቅምና ጉልበት አለው።

በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ እየታዩ ያሉ ችግሮች "ሞልተው የፈሰሱ የዞረ ድምር ውጤቶች ናቸው" የሚሉት ወይዘሮ ሙፈሪያት ትውልዱ ባልሰራውና ባልነበረበት ሊወቀስ አይገባም፤ የእርሱ ያልሆነውን እዳ እየወረሰ መሄድም የለበትም ይላሉ።

በመሆኑም ይህን መሰሉ ሁኔታ ነገም እንዳይቀጥል ዛሬ መነጋገር፣ ይብቃ ማለትም ተገቢ ነው ባይ ናቸው - የሰላም  ሚኒስትሯ።

መልካም እሴቶች ደግሞ ግጭትን የመከላከል ብቻ ሳይሆን ዘላቂ ሰላምን የመገንባት አቅም እንዳላቸው ገልጸው ያሉትን ማዳበር ብቻ ሳይሆን ወቅቱ ከደረሰበት ሁኔታ አንጻር ኢትዮጵያዊነትን የሚያከብሩ ተጨማሪ መልካም እሴቶች መገንባት እንደሚገባም ይመክራሉ።

"ህብረተሰቡ ጠንካራ እሴት መገንባት ካልቻለ ማንም ወደፈለገበት አቅጣጫ የሚዘውረው ይሆናል" የሚሉት ሚኒስትሯ መልካም እሴቶችን ማዳበር ለነገ የሚባል ተግባር እንዳልሆነ ያስገነዝባሉ።

እያንዳንዱ ዜጋ በእሴት ግንባታዎች ላይ ትልቅ ሚና አለው የሚሉት የሰላም ሚኒስትሯ "ምናገባኝ ሳይሆን ምንድነው ያጎደልኩት የሚል ጥያቄ ነው ህብረተሰቡ መጠየቅ ያለበት" ይላሉ።

በተለይም ከመሰረቱ የተቃና ትውልድና አስተሳሰብ ለመቅረጽ ቤተሰብ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፤ መምህራንም ከወላጅ ባልተናነሰ ተጽዕኖ ፈጣሪ በመሆናቸው በትኩረት ሊሰሩ ይገባል አገር የሚመራው እነርሱ የሰሩት ትውልድ ነውና ብለዋል።

ይህ ሲሆንና በመንግስት ደረጃም የተሻለ ስራ ሲሰራ ዘላቂ ሰላም መገንባት ይቻላል ነው ያሉት ሚኒስትሯ።

Comments
* The email will not be published on the website.
I BUILT MY SITE FOR FREE USING