በግብጽ በሚገኘው የአርሰናሉ አማካይ ሞሐመድ ኤልኒኒ መኖሪያ ቤት ውስጥ የአንድ ግለሰብ አስክሬን መገኘቱ ተነገረ።
ከካይሮ 100 ኪ.ሜ. በምትርቀው ማሃላ አል-ኩባር ከተማ በሚገኘው መኖሪያ ቤት አስክሬኑን ቀድመው የተመለከቱት የእግር ኳሰኛው ወላጅ አባት ሲሆኑ ጉዳዩን በፍጥነት ለፖሊስ አመልክተዋል።
ፖሊስ እንደሚለው ከሆነ ሟቹ የኤሌክትሪክ ገመዶችን ከመኖሪያ ቤቱ ለመስረቅ ሙከራ ሲያደርግ በኤሌክትሪከ ተይዞ ለሞት ሳይዳረግ አልቀረም።
መኖሪያ ቤቱ በኤልኒንይ ወላጆች አማካኝነት ለአንድ በጎ አድረጎት ድርጅት ሊሰጥ በዝግጅት ላይ እንደነበረ ተነግሯል።
ከግብጽ ብሔራዊ ቡድን ጋር ካይሮ የነበረው ኤልኒኒ የአፍሪካ ዋንጫ ጉዞውን አጠናቆ ወደ ሰሜን ለንደን ክለቡ አርሰናል ተመልሷል።
ኤልኒን በመኖሪያ ቤቱ ስላጋጠመው አደጋ በስልክ ተነግሮታል ተብሏል።